
ይህ መጽሐፍ ለምን አስፈለገ?
ስለልጅ አስተዳደግ ብዙ መጽሐፎች ተጽፈዋል። ይህንን መጽሐፍ የተለየ የሚያደርገው በጣም ቀላል፣ ለማንበብ የማይሰለች፣ ተግባር ተኮር እንዲሁም ከእያንዳንዱ ገጽ ጠቃሚና ተግባር ላይ ሊውል የሚችል ፍሬ ነገር የያዘ መሆኑ ነው።
ስለ መጽሐፉ
ይህ መጽሐፍ ለምን አስፈለገ? ልጆችን በአካል፣ በእውቀት፣ በስነ-ምግባርና በፍቅር በማሳደግ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለኅብረተሰብ ጠቃሚ ዜጎች እንዲሆኑ ማብቃት ቀላል ሥራ አይደለም። ነገር ግን ይህ ኃላፊነት ለተወሰኑ ቡድኖች ብቻ የሚተው ሳይሆን ከእያንዳንዱ ወላጅ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። አብዛኛው ወላጅ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ሌት ተቀን ይደክማል። ሆኖም ግን ምን ያህሉ ወላጅ፤ በምን ደረጃ ተሳክቶለት ይሆን?
ይህ ስኬት በብዙ ድካም ብቻ የሚመጣ አይደለም፤ ዝም ብሎ ስለልጆች እያሰቡ በመጨነቅም አይመጣም። በድካም እና በጭንቀት ብቻ የሚመጣ ቢሆንማ ኖሮ የሁላችንም ልጆች ጥሩ ሁኔታ ላይ በተገኙልን ነበር። በዚህ ፈንታ ግን አንዳንድ ልጆች ወደ አልተገባ መስመር ሲሄዱ እናያቸዋለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ በእኛ እና በልጆቻችን መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ በመሆን ፈንታ ክፍተት ያለው ወይም የሻከረ ሆኖ እናገኛለን።
ይህ ልጅ የማሳደግ ስኬት ከጥረትና መድከም ባለፈ የሚፈልገው አንድ ወሳኝ ነገር አለ፤ ይህም ወሳኝ ነገር ዕውቀት ነው። ዕውቀት ስንል ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ማለታችን አይደለም። ዕውቀት ስንል የወላጅነት ኃላፊነቶቻችንን በተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚያስፈልጉን ጥቂት መሠረታዊ የሆኑ ግንዛቤዎች ማለታችን ነው። ብዙ ወላጆች ይህ ግንዛቤ የለንም። በተጨማሪም የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት በቂ ዕውቀት ሳንጨብጥ ልጆቻችንን እያሳደግናቸው እንደሆነ እንኳን እናውቀውም። ሌላው ቢቀር ድካማችን የፈለግነውን ውጤት ሳያፈራ ሲቀር ስናይ እንኳን ምን ማስተካከል እንዳለብን አናውቅም። ከዚህ አንፃር ብዙ ወላጆች ልጆቻችንን ባልነቃ አእምሮ ማለትም በዘልማድ ነው የምናሳድገው ማለት ይቻላል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው እንደዚህ ላለን ወላጆች ነው። ዓላማውም ቀላል እና ተግባራዊ በሆነ መንገድ የወላጅነት ኃላፊነታችንን በበቂ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ግንዛቤዎች ማስጨበጥ ነው። ይህ አይነቱ እውቀት የሚያስፈልገንም ከዘልማድ አልፈን የነቃን ወላጆች እንሆን ዘንድ እንዲረዳን ነው።
ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዛት ያጋጠሙኝ እና ያስተዋልኳቸው ክስተቶች ናቸው። በሙያዬ ነርስ ነኝ። በዚህ መስክ ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት ከሆስፒታል እና ከነርሲንግ ማስተማር ሥራዬ ውጪ በማኅበረሰቡ ውስጥ እየሄድኩኝ ብዙ ቤተሰቦችን እጎበኛለሁ፤ እንዲሁም አስተምራለሁ። በዚህ አይነቱ አጋጣሚ በተደጋጋሚ ያስተዋልኩት ምን ያህል ወላጆች ልጆቻቸውን በሚገባ መንገድ ለማሳደግ እየተቸገሩ አንደሆነ ነው። ልጆቻቸው እየተበላሹባቸው የሚያለቅሱ ብዙ ወላጆች አጋጥመውኛል። ታሪካቸውን ስሰማ ደጋግሜ አዝናለሁ፤ ልቤም ይነካል። እኔ እግዚአብሔር ረድቶኝ ሁለት ልጆች በጥሩ ሁኔታ አሳድጌያለሁ። ልጆቼም ራሳቸውን በሚገባ እንዲችሉ፣ በጥሩ ስነምግባር የታነፁ እንዲሆኑና እነርሱም በተራቸው ኃላፊነትን እንዲሸከሙ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ። ታዲያ ያጋጠሙኝን ወላጆች ድካም እና ጭንቀት ሳይ እኔ በትምህርት እና በልምድ ያገኘሁትንና ለኔ የሠራልኝን ጠቃሚ ነገሮች ማካፈል ግድ ሆኖ ተሰማኝ። ስለዚህም ነው፤ ይሄንን መጽሐፍ ለመጻፍ የተነሳሳሁት።
ስለልጅ አስተዳደግ ብዙ መጽሐፎች ተጽፈዋል። ይህንን መጽሐፍ የተለየ የሚያደርገው በጣም ቀላል፣ ለማንበብ የማይሰለች፣ ተግባር ተኮር እንዲሁም ከእያንዳንዱ ገጽ ጠቃሚና ተግባር ላይ ሊውል የሚችል ፍሬ ነገር የያዘ መሆኑ ነው። ማንኛውም ወላጅ ከዚህ መጽሐፍ ብዙ ጠቀሜታ ያገኝበታል ብዬ አምናለሁ።
መጽሐፉ በሦስት ክፍል ተዋቅሮ የቀረበ ነዉ። የመጀመሪያው ክፍል ልጆች በተለያዩ የዕድሜ ክፍሎች ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤና ትኩረት የያዘ ነው። እነዚህም ከ0-1፣ ከ1-3፣ ከ3-6፣ ከ7-11 እና ከ12-18 ዓመታት በዕድሜ ተከፋፍለው ቀርበዋል። ይህ ክፍል በእነዚህ የዕድሜ ክልሎች ውስጥ ያሉ ልጆቻችን ከእኛ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ምን እንደሆነ ተረድተን አቀራረባችን በዚህ ግንዛቤ መሠረት እንድናደርግ ይረዳናል። ሁለተኛው እና ሦስተኛዉ ክፍሎች ደግሞ ርዕስ ትኮር ናቸዉ። እነዚህ ክፍሎች ደግሞ ልጆቻችንን በተመለከተ በሃያ ስድስት (26) ርዕሶች ላይ ምክር እና መመሪያ ይሰጣሉ።
ከዚህ መጽሐፍ እንደ ወላጅ ብዙ ጥቅም ታገኙበት ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው! በማንበብ፣ በማጥናትና በሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ባግባቡ በማሰብ በየትኛውም ደረጃና አውድ የሚገኙ ልጆቻችንን በተሳካ መልኩ ለማሳደግ ራሳችንን በእውቀትና በክህሎት እንድናንጽ አደራ እላለሁ።
ሣራ ዘመኑ ሰናይ